🔇Unmute
አዶላ፤ ግንቦት 4/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በዘንድሮው ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ18 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ መቅረቡን የዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ልዩ ጣዕም ያለውን ቡና በማምረት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ ከሚገኙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ የጉጂ ዞን ነው።
በዞኑ አብዛኛው የቡና ልማት በተፈጥሮ ደኖች ጥላ ስር የሚከናወን በመሆኑ፣ ምርቱ ተፈጥሯዊ (Organic) ይዘቱን ሳይለቅ እንዲያድግ ይረዳዋል።
በዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት የእቅድና በጀት ባለሙያ ደረሰ ደንቆ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ከዞኑ ከ75 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
በዞኑ የሚገኙ 36 የቡና ምርት አቅራቢዎች ምርቱን በብዛትና በጥራት እያዘጋጁ ለማእከላዊ ገበያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 18 ሺህ 682 ቶን ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ታጥቦ የተቀሸረ ደረቅ የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ መቅረቡን ገልጸዋል።
ዘንድሮ ለገበያ ለማቅረብ የታቀደው ምርት ከዓምና ጋር ሲነጻጸር እድገት ማሳየቱንም ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በዞኑ የቡና ጣእም ቅምሻ ማእከል መቋቋሙን ገልጸው፤ ማዕከሉ የቡና ምርት ጥራትና ብዛትን በመጨመር በአምራቾች ዘንድ መነሳሳት መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።
በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የቡናና ሻይ ልማት ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ በበኩላቸው የቡና ልማቱን ለማስፋት የተሻለ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ እየቀረበ ይገኛል።
በዚህ ዓመት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅሰው፣ በልማቱም ከ108 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የአዶላ ከተማ ነዋሪና የቡና አምራች አቶ ጌታቸው ጎልጃ በሰጡት አስተያየት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተሻሻለው የቡና ልማትና ግብይት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የቡና ጣእምና የቅምሻ ማእከል በአካባቢያቸው መቋቋሙን ተከትሎ የቡና ምርቱን በብዛት እና በጥራት በማምረትና ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል።
ሌላው የቡና አቅራቢ የሆኑት አቶ ኤልያስ ሰንጋጎ ከዘርፉ ገቢያቸውን ለማሳደግ ለምርት ጥራት ትኩረት መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
የጉጂ ዞን ከ377 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተከል መሸፈኑ ታውቋል።
微信扫一扫 立即联系我们