🔇Unmute
ጂንካ፤ ግንቦት 4/2018 (ኢዜአ):-ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ኦሞ-ቱርካና የተሰኘ የምርምር ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
ከምስራቅ አፍሪካ የምርምር ማዕከላት፣ ከኢጋድ፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ሚኒስቴር የተውጣጡና ሌሎችም በተገኙበት የ''ኦሞ-ቱርካና የምርምር ማዕከል" ለማቋቋም የሚያስችል የምክክር መድረክ ዛሬ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ተስፋዬ አለሙ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ባሻገር በጥናትና ምርምር ለማህበረሰብ ለውጥና ተጠቃሚነት እየሰራ ይገኛል።
ይህን ስራውን ለማጠናከር በኦሞ ወንዝና በቱርካና ኃይቅ አቅራቢያ ዩኒቨርሲቲው የ''ኦሞ-ቱርካና የምርምር ማዕከል'' ሊገነባ መሆኑን አስታውቀዋል።
ማዕከሉ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ከመፍታት አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ለሚከሰቱ ችግሮች በሳይንሳዊ ጥናት የታገዘ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስችል ጠቅሰዋል፡፡
የምርምር ማዕከሉ በኦሞ ሸለቆ ያለውን ዕምቅ የብዝሃ ህይወት አቅም አውጥቶ ለመጠቀም እና ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለማካሄድ ጭምር ያግዛል ብለዋል።
በዳሰነች ወረዳ ሁለት ሄክታር መሬት ላይ በሚቋቋማው በዚህ ማዕከል ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ከሀገራት የምርምር ማዕከላትና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ለችግሮች የጋራ መፍትሔ ይመነጭበታልም ተብሏል።
የምርምር ማዕከሉ ግንባታ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ግንባታው የሚከናወንበትን ቦታ ከማመቻቸት ጀምሮ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳትና ዓሣ ሀብት፣ በብዝሃ-ህይወት፣ በብዝሃ-ባህል እንዲሁም በአግሮ ኢንዱስትሪ ላይ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ማዕከሉም በእዚህ ዘርፎች ለውጥ ማምጣት የሚያስችል የምርምር ውጤቶች የሚፈልቁበት ይሆናልም ተብሏል።
微信扫一扫 立即联系我们